ይህንን ስትሰሙ ምን አላችሁ!
መቼም አሁን አሁን የምንሰማቸው ነገሮች ከባሕላችንና ወጋችን የወጡ ድርጊቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ከእኛም አልፎ ዓለምን ጉድ የሚያሰኙ አሳዛኝ የወንጀል ድርጊቶች በሀገራችን እየተለመዱ ሂድዋል። በዚህ ጉዳይ ብዙ ብዙ ማለት የሚቻል ቢሆንም፣ ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያክል እንደሚከተለው ተመልክተናል። ቤተሰቡ ለልጆቻችን እንደ ሞግዚት፣ ለንብረታችን ጠባቂና ባለ አደራ ትሆንልናለች ያላትን ሠራተኛን አፈላልጎ መቅጠር ነበረበት፡፡ በዚህም የተቀጠረችውም ሰራተኛ ቤተሰቡ ንብረቱን ቤቱን ከምንም በላይ ደግሞ እጅግ አብዝቶ የሚሳሳላቸውን እንቦቀቅላ ሕፃናቱን ሲርባቸው እንድታጎርሳቸው ሲጫወቱም ሆነ ሲቦርቁ ክፉ ነገር ላይ ወድቀው አደጋ እንዳይገጥማቸው እንድትጠብቃቸው ሞግዚትም ጠባቂም አድርጎ አደራ ብሎ ትቶላት መሄድ ጀመረ፡፡ የቤት ሰራተኛዋ የተሰጣትን ከባድ አደራ ሳያስጨንቃት አደራዋን በልታ ታማኝነትዋን አጉድላ ምንም የማያውቁ እንቦቀቅላ ሕፃናቱን አስደንጋጭ በሆነ በግፍ የመግደልዋን ዜና ሰማን፡፡ በወንጀሉ ተደናግጠን በመራሩጭካኔዋ እጅግ አምርረን አለቀስን እንጂ ልንለው የቻልነው ነገር አልነበረም። ምናልባት ለክፋትዋ ማለስለሻ ለመራሩ ጭካኔዋ ይቅርታ እንድናደርግላት ሊያደርግ የሚችል ባይሆንም እንክዋን ምናልባት ይህንን ድርጊት ለመፈጸም የተነሳሳችበት ምክኒያት፣ በቤተሰቡ ደስተኛ ባትሆን ቤተሰቡ በድልዋት ቢሆን እንኳን ሲሆን ሲሆን የነበራቸው የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት እንደመሆኑ መጠን፣ ከቤተሰቡ ጋር ሰላም ካልሆነች ስራውን ለቃ ሌላ ቦታ ተቀጥራ መስራት ስትችል፤ አለበለዚያ ደግሞ በደልዋን የደረሰባትን ግፍ ለሚመለከተው አካል ተናግራ የሚገባትን ማግኘት ወይም መካስ ስትችል እንዲህ ለጆሮም ለአይንም የከበደ የጭካኔ መርግ ለማውረድ አይደለም ጮህ ብለህ ልትቆጣቸው እንኳን የሚያሳሱ ምንም የማያውቁ እንቦቀቅላ ሕፃናትን ላይ የቂም በቀል መወጣጫ ማድረጉ ቃላት የማይገልጹት የጭካኔ ድርጊት ነው ከማለት በስተቀር ምን ማለት ይቻላል; ብለን አለፍነው።
አባት ልጆቹን ብቻውን ሆኖ ማሳደግ ቢከብደው፣ የእናታቸው ምትክ ሆና ልጆቼን እንዳይከፋቸው ትንከባከብልኛለች ሲርባቸው ቤት ያፈራውን ትመግብልኛለች ልብሳቸው እንዳይቆሽሽ በአጠቃላይ እናታቸውን ባትተካላቸውም በእናታቸው በሞት ማጣት የተፈጠረውን ክፍተት እንደ እናት ሆና ትንከባከብልኛለች ብሎ ያገባት ሚስት እርስዋኑ አምኖ ወደ ስራ ቢሄድ በአደራ የተሰጥዋትን ልጆች በተኙበት አሰቃቂ በሆነ የግፍ አገዳደል መፈጸምዋን ስንሰማ እግዚኦ ምን መዓት መጣብን ከማለት ውጪ ሌላ ልንለው የቻልነው ነገር አልነበረም።
እናት የማሕጸንዋ አብራክ የሆነውን ለዓመታት ክፉ አይንካህ ብላ ያሳደገችው ልጅዋን በመርዝ መግደልዋ ስንሰማ አንተው አውጣን ብለን አለፍነው።
ልጅ ስንት ክፉ ደጉን አይተው ያሳደጉት ሲሆን በስተእርጅናቸው በመጦረና የሚገባቸውን አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ማድረግ የሚችለውን ሊያደርግላቸው ሲገባው፣ የገዛ አዛውንት ወላጅ እናቱን ሰንካላ ምክኒያት ፈጥሮ እጅግ በሚዘገንን የግፍ አገዳደል በተኙበት መግደሉን ስንሰማ በድንጋጤ ክው ከማለታችን እውን ይህንን ያክል የጭካኔ ከፍታ ላይ ወጥተን የስብእና ዝቅተት ወርደን እዚህም ደረጃ ተገኘን ማለት ነው; በማለት ስንቶቻችን በእንባ ተራጭተን አለፍነው። …. እያልን በርካታ ጉዳዮችን ሰምተን ጆሮአችን አረ ሰለቸኝ በቃኝ ብሎ ሳያበቃ አንድ ያልተለመደ አሳዛኝና አስገራሚ በፍርድ ቤት ያውም ችሎት ውስጥ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ሰማን። ጉዳዩ እንዲህ ነው።
እለቱ አርብ ሃምሌ 25/2015 ዓ.ም ቦታው በምስራቅ ሐረርጌ የበደኖ ወረዳ ፍርድ ቤት ባልና ሚስት ከስተጀርባ የነበረው ድብቅ ስሌት ባይታወቅም፣ የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮዋ የባላቸውን በሞት መነጠቅ ተከትሎ ብቸኝነቱ ቢከብዳቸው የኑሮ ሸክም ለብቻ ሆኖ ቢፈትናቸው ልጆቼን በማሳደግ ይረዳኛል በሚል መንፈስ ከአንድ ሁለት ሳይሻል አይቀርም በሚል ይመስላል የኑሮ የሕይወቴ አጋር ይሆነኛል ትሆነኛለች ተባብለው ሁለተኛ ባል አግብተው ጎጆ ቀልሰው ትዳር በሚባለው ጥላ ስር ተጠልለው መኖር ጀመሩ።
ነገር ግን አንድ አንዴ ነገሮች እንደታቀዱት እንደሚሄዱ ሁሉ አንድ አንዴም እንዳሰቡትና እንዳቀዱት አይሆንም። ሁለተኛ ትዳር የመሰረቱት ወይዘሮ ትዳራቸው የሰመረ ትዳር ከመሆን ይልቅ አለመግባባትና ንትርክ በዝቶበት አስከፊ ትዳር ሆነባቸው። እንዳሰቡትና እንደተመኙት አንዱ የሌላው የሕይወት አጋር የኑሮ ረዳት ሊሆኑ ሳይችሉ ቀሩ። አዲሱ ትዳር አልሆን ቢላቸው ባልና ሚስት ጥምረታችን ልክ አልነበረምና ለዚህስ ብቸኝነቱ ምን አለን በሚል መንፈስ ትዳራችን ቢያበቃስ በሚል ጉዳያቸውን ፍርድቤት ድረስ ይዘውት ለመሄድ ተገደዱ።
ፍርድቤትም እንግዲህ አበሮ መኖሩ ካላዋጣችሁ ለየብቻችን ይሻለናል ካላችሁ ምን ማድረግ ይቻላል ይልና ፍቻቸውን በሕጋዊ መንገድ አጸደቀው። በቀጣይነት የሚኖረው የንብረት ክፍፍል ነው። የምትስማሙትን ተስማምታችሁ የማትስማሙበትን ደግሞ ለእኔ ይገባል የምትሉትን ዘርዝራችሁ ከማስረጃ ጋር አቅርቡልኝ ሲል ትእዛዝ ይሰጣል።
ሁለቱም ይገባናል የሚሉት አለን ከሚሉት ማሰረጃ ጋር እንደ ትእዛዙ ለፍርድቤቱ አቀረቡ። ፍርድቤቱም የቀረበለትን የንብረት ዝርዝርና ማስረጃ በማገናዘብ ፍትሓዊ ነው ያለውን ውሳኔውን ሰጠ። በዚህ ሁሉ ሂደት በአጉል የንዋይ ፍቅር የተሳቡት አቶ ባልም፣ ደስታሽ ደስታዬ ሀዘንሽና መከፋትሽም ተጋርቼ ከጎንሽ ለመቆም ፈቃደኛ ነኝ ብለው ያገብዋቸውው ሚስት ከልብ ሳይሆን ያላቸውን ሀብትና ንብረት በትዳር ስም ለመንጠቅ ነበር መሰል በፍርድ ሂደቱ በገናው ተሸናፊ መሆናቸውን አስቀድመው ያወቁት ይመስላል። በዚህም የተነሳ በውሳኔውም ፍርድ ሂደቱም ደስተኛ የነበሩ አይመስሉም። እናማ ቂም ቋጥረው ወንጀል ድርጊታቸውን አውጥተው አውርደው ለእቅዳቸው መፈጸሚያ ቦታና ስፍራ መርጠው ጊዜውንም ወሰኑ። አስገራሚው ነገር የወንጀል እቅዳቸው የሚፈጽሙበት ጊዜና ቦታ ምርጫቸው ነበር። የውጀል ድርጊታቸውን ለመፈጸም ያቀዱት ውሳኔ በሚያገኝበት እለት ቦታው ብዙዎቹ በሚያከብሩት ብቻ ሳይሆን ፈርተው በሚንቀጠቀጡበት የፍርድ አደባባይ ያውም በችሎት ውስጥ ለመፈጸም ወደዱ።
የወንጀል ድርጊታቸውን ለመፈጸም ያቀዱትም እቅዳቸው ከቀናቸውና ከሆነላቸው በፍርድ እንደሚረትዋቸው እርግጠኛ የሆኑትን በፍቺ የተለይዋቸውን የቀድሞው ሚስታቸው የአሁኑ ባላጋራቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ፍርድ የሰጡት የተከበሩ ዳኛው ላይም መሆን እንዳለበት ድምዳሜ ላይ ደርስዋል።
በእቅዳቸውም መሰረት ለእቅዳቸው መፈጸሚያ መሳሪያ አዘጋጅተው በእለቱና በሰአቱ በቦታው ተገኝትዋል።
በፍርድቤቱ ያለው ሁኔታ የተለመደ ነው። ባለጉዳዮች ይገባሉ ይወጣሉ። የፍርድቤት ሰራተኞችም የተለመደውን ድርጊታቸውን በማከናወን ላይ ናቸው። መዝገብ በማመላለስ ላይ ታች ይላሉ፤ ዳኞች የሚሰጥዋቸውን ቀነቀጠሮዎች ይመዘግባሉ የሚሰጡትን ትእዛዞች ለሚመለከታቸው አካላት እንደ ትእዛዛቸው እንዲፈጽሙ ያስተላልፋሉ።
ዳኛውም እንዲሁ የዘወትር ስራቸውን በማከናወን ላይ ናቸው። አዳዲስ የክስ ማማመልከቻዎችን ይቀበላሉ አስፈላጊ ያሉትን ትእዛዝ ይሰጣሉ ባለጉዳዮችን ይቀጥራሉ ምስክሮችንም ይሰማሉ ማስረጃዎችንም መርምረው ተገቢ ነው ያሉትን ትእዛዝ ይሰጣሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ የባልና ሚስት ውሳኔ የሰጡበትን መዝገብ ከፊት ለፊታቸው ቀረበላቸው። በቀጠሮአቸው መሠረት ተከራካሪ ወገኖች ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ትእዛዝ ይሰጣሉ። በትእዛዛቸው መሠረት የችሎት አስተናባሪዋ የባለጉዳዮችን ስም ስትጠራ ስማቸው የተጠሩ ባለጉዳዮች በቀጠሮአቸው መሰረት መገኘታቸውን አረጋግጠው በዳኛው ፊት ተገኝትዋል።
ንብረቴ ያለ አግባብ ሊወሰድብኝ አይገባም በማለት የሚከራከሩት ወይዘሮዋ ምንም እንክዋን የትዳር አጋሬ ይሆነኛል ልጆቼን በማሳደግ ይረዳኛል ብለው ያገብዋቸው ሁለተኛው ባላቸው በትዳሩ መፍረስ ከምንም በላይ ደግሞ በንብረቱ ክፍፍል አምርረው እንደጠልዋቸውና ጉዳት እንደሚያደርሱባቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ሲዝቱና ሲፎኩሩባቸው እንደነበር ቢያውቁም ያሉበት ቦታ ሕግ የሚከበርበት ደህንነቱም አስተማማኝ የሚባል ስፍራ ከመሆኑ አንጻር አደጋ ይገጥመኛል ችግር ይፈጥርብኛል ብለው ሊጠራጠሩ ቀርቶ ሊያስቡት እንክዋን የቻሉ አይመስሉም። እናም በችሎቱ ቁመው የዳኛውን ውሳኔ በጽሞና ያዳምጣሉ።
ባልየው ዝግጅታቸውን ጨርሰው፣ ጥርሳቸውን ነክሰው የልባቸውን በልባቸው ይዘው ተዘጋጅተው ከዚህ በፊት “ውዴ! ባለቤቴ!” እያሉ ሲጠርዋቸው ከነበሩት የቀድሞው ሚስታቸው የአሁኑ ባላጋራቸው ጎን ቆመው የዳኛውን የመጨረሻ ውሳኔ ያዳምጣሉ።
ዳኛው ቢያንስ በዚህ ስፍራ በዚህ ቦታ እንዲህ አይነት ድርጊት ይፈጸማል ብለው ለመጠርጠር አይደለም ለማሰብ እነክዋን የቻሉ አይመስሉም እናም ሀገር ደህና ብለው የተለመደ ስራቸውን ቀጥለው በመዝገብ ቀጠሮቸው መሰረት ባለጉዳዮች መገኘታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የጉዳዩ አይነት በመግለጽ፣ ተከራካሪ ወገኖች ያነስዋቸውን የክርክር ጭብጦችና ያቀረብዋቸውን ማስረጃዎች በዝርዝር ካቀረቡ በኋላ ማስረጃዎችን መዝኖ ፍርድቤቱ የደረሰበትን መደምደኒያ በንባብ በማሰማት ላይ ናቸው።
“በዚህም መሰረት” አሉ ዳኛው “ተከራካሪዋ ወይዘሮ ለክርክር የቀረበው ንብረት የግላቸው ንብረት ለመሆኑ በማስረጃ አስደግፈው የተከራከሩ በመሆኑ ፍርድቤቱ ቀኝና ግራ ያቀረብዋቸውን ማስረጃዎችን በመመዘን ንብረቱ የወይዘሮዋ ንብረት መሆኑን ወስንዋል።” በማለት በውሳኔው ቅር የተሰኘ ወገን ይግባኝ የማለት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ገልጸው ውሳኔያቸውን አሰምተው ጨረሱ።
በዚህን ጊዜ አቶ ባል እቅዳቸው የሚፈጸምበት ሰአት ባወጡት የወንጀል እቅድ መሠረት ወደ ድርጊት መግባት እንዳለባቸው ወሰኑ።
በዚህም መሠረት ሰውየው የፍርድቤቱን የችሎት አዳራሽ በቅጽበት ከእውነተኛ ችሎት ወደ ፊልም ወይም የቲያትር መድረክ ወደሚመስል ልዩ ትእይንት የሚታይበት ቀየሩት። ሰውየውም ልክ እንደ አንድ የመድረክ ተዋናይ በሚመስል ሁኔታ ውሳኔውን መቀበላቸውን በሚገልጽ ምልክት ወደ የቀድሞ ሚስታቸው የአሁኑ በፍርድ የረትዋቸው ወይዘሮ ተጠጉ። እንደተጠግዋቸውም፣ ደብቀው ይዘውት የገቡት ስለት መዘው በማውጣት በቀድሞው ሚስታቸው በአሁኑ ባላጋራቸው ደረት ላይ በመሸቅሸቅ ያልታሰበ ብቻም ሳይሆን ሊታሰብም የማይችል እኩይ ድርጊት ፈጸሙ።
ይሄኔ ወይዘሮዋ አስደንጋጭና ሰቅጣጭ ጩሄት አሰምተው የተወጋው ደረታቸው በመያዝ አጎነበሱ ወንጀለኛው ወይዘሮዋን ባጎነበሱበት ወቅት ጀርባቸውን በድጋሜ ወግዋቸው።
በሰሙት ያልተለመደ ጩሔት ተደናግጠው ከመዝገባቸው ቀና ያሉት የእለቱ ዳኛም የሰሙትና የተመለከቱትን ማመን አልቻሉም። ዘለው ከችሎት ወንበራቸው ተነስተው ወንጀለኛው ከድርጊቱ ለማስቆም ተንደረደሩ። ወንጀለኛ ይህም ሲፈልገውና ሲጠብቀው የነበረ በመሆኑ የስለት መሳሪያውን ወደ ዳኛው አምዘገዘገው። ወንጀለኛው የልቡ አልደረሰለትም ምክኒያቱም ስለቱ ዳኛውን ስቶቸው በመውደቁ ሊያገኛቸው አልቻለም።
በዚህን ጊዜ በአከባቢ የነበሩ የጸጥታ አካላት ደርሰው ወንጀለኛውን በቁጥጥር ስር በማዋል ተጨማሪ ወንጀል ሳይፈጽም ወደ ማረፊያ ቤት፤
ዳኛውንም ከተጨማሪ ጥቃት፤
ስፍራውንም ከወንጀል መፈጸሚያነት ስፍራ ወደ የተለመደው የሕግ ልዕልና የሚከበርበት ስፍራ፤
ተጎጂዋን ደግሞ የሕክምና እርዳታ ወደ ሚያገኙበት ሀኪም ቤት ወሰድዋቸው። ይሁን እንጂ የጸጥታ አካላቱ ይሄኛው ሊሳካላቸው አልቻለም ተጎጂዋ ሃኪም ቤት ቢያደርስዋቸውም በሕይወት ለመትረፍ አልቻሉም።
አስገራሚው፣ ነገር ግን ደግሞ እጅግ አሳዛኙ የወንጀልና የፍርድ ሂደት በዚህ መልኩ ተጠናቀቀ።፡
ያሳዝናል ፍርድቤቱ ይሁኑ ዳኛው የወይዘሮዋን የንብረት መብታቸውን ቢያስከብርላቸውም፣ ሕይወታቸውን ግን ሊታደግላቸው አልቻሉም። ወይዘሮዋም ተከራክረው በፍርድ ቢረቱም የፍርድ ሂደቱ ግን ደህንነታቸውን ሊታደጋቸው አልቻለም።
ጋዜጦችና ሚዲያዎችም የእለቱ የፍርድ ትእይንት በሚከተለው ዘገቡት
#በችሎት ፊት በስለት ተወግታ ተገደለች!
#ፍትሕ እስከ መቃብር!
#የሞት ዛቻ ያልገደበው የፍትሕ ጥያቄ!
#የሁለት ልጆች እናት በችሎት ፊት በባሏ በስለት ተወግታ ሞተች! … እያሉ ዘከርዋቸው። እኒህ ሴት ሕይወታቸውን የገበሩት ለእውነትና ለፍትሕ በሚያደርጉት ሙግት ነው። ይህ የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ፍትሕ የተነፈጉ የብዙ ሴቶች ግፍና መከራ ተምሳሌት ነው። ስንቶቹ በገዛ ባሎቻቸው በግፍ ተገድልዋለል፤ ስንቶቹስ የእኔ ነው ባሉት አካላቸው ጎድልዋል፤ ስንቶቹስ አሲድና ከሚካል ተደፍቶባቸው መልካቸው ጠፍቶ ስነ ልቦናቸው ተሰብሮ እንዲኖሩ ተገድዋል። ታዲያ እኒ እናትም የክፉ ቀን ደራሼ በክፉም በደግም ከጎኔ ይሆንልኛል ባሉት ሰው በፍትሕ አደባባይ የግፍ አገዳደል ተገድልዋልና እዚያው ፍርድቤት ውስጥ ያውም በተገደሉበት ችሎት ውስጥ ሃውልት ቢቆምላቸው ሕይወታቸውን ባይመልስላቸው እንክዋን ለቤተሰቦቻቸው በተለይም ደግሞ ለልጆቻቸው መጽናኛም ማስታወሻ ይሆንላቸዋል ባይ ነኝ። ከዚህ በተጨማሪም የማሕበረሰቡን የሕሊና ደወል ሆኖ እንዲህ አይነት የግፍ አገዳደል በሴት እሕቶቻችን፣ እናቶቻችን ብሎም ልጆቻችን ላይ ይብቃ ይቁም እንዲል የሚቀሰቅስ ነው ብዬም አስባለሁ። እናም ለዚህች ፍትሕ ሲሉ ለሞቱት ሚስኪን እናት ሃውልት ቢቆምላቸው የሚያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም።
ተከሳሹ በቁጥጥር ስር ያዋለው ፖሊስ ግለሰቡን ለፍርድ እንዲቀርብ በማድረግ ጉዳዩን በከፍተኛው ፍርድቤት ሲከታተል ከቆየ በኋላ ጥቅምት 5/2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን በእድሜ ልክ እንዲቀጣ ወስኖበታል።
አቃቤ ሕግ በክስ ማመልከቻው ለፍርድቤቱ እንደገለጸው ከሆነ ግለሰቡ የወንጀል ድርጊት በተፈጸምበት ችሎት አካባቢ የነበረ የፖሊስ አባል ግለሰቡን ሊያስቆም በሞከረበት ጊዜ እሱንም በስለት ሊወጋው ሞክሮ እንደነበረም ተገልጿል።
በቀድሞ ባለቤቱ ግድያ በከባድ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሰው ግለሰቡ፣ በተጨማሪም በሕግ አስከባሪ ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ፣ ችሎት በመረበሽ እና የመንግሥት ሥራን ማደናቀፍ በሚሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ክሶች ቀርበውበታል።
የሚገርመው ነገር ደግሞ ተከሳሹ ድርጊቱ በፍርድቤት ያውም ችሎት ውስጥ ፈጽሞ ሲያበቃ የተከሰሰበትን ወንጀል እንዳልፈጸመ ቃሉን በመስጠት ከመከራከሩም በላይ ምስክሮችን በማቅረብ ከቀረቡበት አምስት ክሶች ራሱን ለመከላከል ሞክሮ ነበር።
ይሁን እንጂ ግለሰቡ ያቀረባቸው ምስክሮች ድርጊቱ ሲፈጸም በስፍራው ያልነበ እና ስለወንጀሉ የማያውቁ በመሆናቸው፣ የቀረቡበትን ክሶች በተገቢው ሁኔታ ለመከላከል የሚያስችለው ማስረጃ አላቀረበም በሚል ፍ/ቤቱ ጥፋተኛ ነህ የሚል ውሳኔ ሰጥቶበታል።
ነገሩ በሕግ ፊት ያውም ፍርድቤት መሆኑ በጀ እንጂ በሌላ ስፍራ ቢሆንማ ኑሮ እንዴት አይነት የተቀናበረ የሀሰት ምስክርነት ሊያቀርብ እንደሚችል መገመት ይከብዳል።
የችሎቱ ዳኛ በተከሳሹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ እንዳለበት በማመልከት ቅጣት ማክበጃ ለፍርድ ቤቱ እንዳቀረበ ተገልጽዋል።
በመጨረሻ ችሎቱ ተከሳሹ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያን ውድቅ በማድረግ በቀድሞ ሚስቱ ላይ በችሎት ፊት በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል ክስ እና በተያያዥ ክሶች የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶበታል። በሞት አለመቀጣቱ እድለኛ ነው። ምክኒያቱም ሆን ብሎ አስቦበት ተዘጋጅቶበት ያውም ፍርድቤት ውስጥ ፍትሕ የሚሰፍንበት የወንጀል ድርጊት መፈጸሙ ለሕግ ያለውን ንቀት ለችሎቱ ያለው ንቀት በመግለጽ ለሕግ ተገዢ አለመሆኑ አንደኛው ምክኒያት ሲሆን በድርጊቱም ምንም አይነጸጸት ያልተሰማው መሆኑን ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ለመከራከር ሞክርዋል። ቢሆንለት ኑሮ ሕግና ፍትሕን ለማሳሳት ለማጭበርበር ሞክሮ ነበር።