የቤተሰብ ምሥረታ:

ስለቤተሰብ ስናነሳ፣ ቤተሰብ የአንድ ማሕበረሰብ መሠረት መሆኑን ከዚህ በፊት የሰጠናቸው ሓተታዎች ያመለክታሉ። ታዲያ የማሕበረሰቡ መሠረት የሆነው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሚኖሩበት ስብስብ እንዴት ይመሰረታል የሚለውን መመልከቱ አስፈላጊ ነው። ቤተሰብ የሚመሰረተው አንድ ወንድና አንዲት ሴት በትዳር አብሮ ለመኖር በሚያደርጉት ስምምነት በሚፈጠር ጥምረት ነው። ይህ ስምምነት ደግሞ ጋብቻ ይባላል። በመሆኑም፣ የቤተሰብ መሠረቱ ጋብቻ ነው። ጋብቻው ከተመሰረተ በኋላ በወንዱና በሴቲቱ መካከል ራሱን የቻለ ዝምድና ተፈጠረ ማለት ነው። ዝምድናውም የጋብቻ ዝምድና የሚባለው ነው፡፡ ይህ የዝምድናው መፈጠር ተከትሎ ሌሎች ቤተሰብን የሚያጠናክሩ እንደ ልጆችና ሌሎች ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወደ ጎን የሚቆጠሩ ቤተሰብን የሚያስተሳስሩ እንደ ድርና ማግ የተዋሃዱ የዝምድና ድር የቤተሰብ ስብስብ እንዲፈጠር ምክኒያት ይሆናሉ። ዋናው መሠረት ግን ባልና ሚስት በሚያደርጉት ስምምነት ነው። በመሆኑም የቤተሰብን ስረ-መዋቅር ከመመልከታችን በፊት ለመናገር ጋብቻ ምንድነው የጋብቻ አላማዎች ምንድናቸው የሚሉትን አንስቶ ማየቱ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ማንኛውም እድሚያቸው የፈቀደላቸው (ለአካለ መጠን ያደረሱ) ወንድና ሴት ጋብቻ የመመሥረት መብት እንዳላቸው በሕግ ተደንግግዋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ጋብቻ፥ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ቤተሰብ መስርተው በትዳር አብሮ ለመኖር የሚያደርጉት ነጻ ስምምነት ነው። የሚደረገው ስምምነትም, በክብር ሹም ፊት ቀርቦ በማረጋገጥ ሊሆን ይችላል አልያም ደግሞ እንደ እምነታቸው በሃይማኖት ስርአት መሰረት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ የአከባቢያቸውን ባሕል መሰረት በማድረግ በትዳር ተጣምረው ለመኖር የሚያደርጉት ስምምነት ነው። ስለዚህ ጋብቻ ተፈጽሞ ቤተሰብ ተመሠረተ የምንለው አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ጋብቻ ለመፈፀም ተስማምተው በክብር መዝገብ ሹም ፊት በመቅረብ ተጋብተው ለመኖር እንደሚፈልጉ ስምምነታቸውን በነጻ ፈቃዳቸው ሲገልጹ፣ ወይም በሁለቱም ወይም ከሁለቱም በአንዱ በሆነው የእምነት ስነሥርዓት ቀርበው እምነቱን የሚጠይቀውን ፈጽመው ሲጋቡ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአከባቢያቸው ባለው የባሕል ሥርዓት መሠረት የሚፀና ጋብቻ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ሥርዓት ሲፈጽሙ ነው። ተከታታይ ዓጫጭር ጽሑፎች አሉን አብራችሁን ሁኑ፡፡ ለአሁኑ፣ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top